
በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበር ወረዳ መዘዞ ጤና ጣቢያ “ተባብረን የተሻለች ኢትዮጲያን እንገንባ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከ5ሚሊዬን ብር በላይ በሆነ ወጪ 4ክፍል የተመላላሽ ህክምና ክፍል ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል።
በግንባታዉ ከ100ሺህ ብር በላይ ከህብረተሰብ ተሳትፎ መገኘቱም ተገልጿል።
ድርጅቱ ከግንባታዉ ባሻገር ከ319ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የአልትራሳዉንድ ማሽን ገዝቶ ለጤና ጣቢያዉ ማስረከቡንም በምርቃቱ ተገልጿል።
በምርቃት ፕሮግራሙ የጣርማበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል መርሻ የጤና ተቋሙ አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ ለማድረግ ድርጅቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።
ግንባታዉ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድርጅቱ ፣ወረዳዉ እንዲሁም የሚመለከታቸዉ ተቋማት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የጣርማበር ወረዳ ጤና ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ደግአረገ አንዷለም ግንባታዉ ተጠናቆዉ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ የብዙ ህሙማንን ችግር የቀረፈ ነዉ ብለዋል።
የመዘዞ ጤና ጣቢያ ሀላፊ አቶ ሚሊዮን ደመረ በበኩላቸዉ የግንባታዉ መጠናቀቅ የተመላላሽ ህሙማን በተሻለ ቦታ እንዲታከሙ አስችሏል ብለዋል።
የጤና ጣቢያዉን አገልግሎት ለማሻሻል ሌሎች ግንባታዎችንም እየሰራን እንገኛለን ያሉት ሀላፊዉ የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሟሉም ከረጅ ድርጅቶች ጋር በሰፊዉ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
ለግንባታዉ መጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላትና ተቋማት እዉቅና ተሰጥቷል።


