
በሰሜን ሸዋ ዞን በጣርማበር ወረዳ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው የ”ኮድ ኢትዮጵያ” የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት የግንባታ አፈጻጸም 53 በመቶ መድረሱ ታወቀ።
የግንባታውን ወቅታዊ ሂደት በወረዳው ከፍተኛ አመራሮች የተጎበኘ ሲሆን ግንባታዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በጊዜ እንዲጠናቀቁ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
የጣርማበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል መርሻ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹትበወረዳው የሚከናወኑ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ማናቸውም ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ ለማድረግ በየጊዜው የተጠናከረ የድጋፍና የክትትል ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የፕሮጀክቶች በተገቢው ጥራት መጠናቀቅ ለሕዝብ ጥቅም መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የታቀደለት የ”ኮድ ኢትዮጵያ” የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ግንባታ በአሁኑ ወቅት በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
የዚህ ፕሮጀክት የግንባታ ወጪ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ እና በክልሉ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በጋራ የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል።
ግንባታዉ በደብረሲና ከተማ አስተዳደር የቦታ ድጋፍ 02 ቀበሌ ላይ እየተገነባ ይገኛል።
የቤተ-መጻሕፍቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአካባቢው ለሚገኙ ተማሪዎችና ወጣቶች ሰፊ የእውቀትና የማንበቢያ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ቀሪ ሥራዎቹ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ የተጀመረው ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በጉብኝቱ ተገልጿል።
በተመሳሳይ በደብረሲና ጤና ጣቢያ እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎችም በጉብኝቱ ታይተዋል።


