
የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የወፍ ዋሻን የመንግስት ጥብቅ ደን በብሔራዊ ፓርኮች የአስተዳደር ስርዓት እንዲመራ የቀረበውን ጥያቄ አፅድቋል።
የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ተስፋሁን አለምነህ፦ የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን 8732.78 ሄክታር ስፋት ያለው በአንኮበር፣ በባሶና ወረና እና ጣርማ በር ወረዳዎች በሚገኙ 15 የገጠር ቀበሌዎች የሚዋሰን የመንግስት ደን መሆኑን ገልፀዋል።
ጥብቅ ደኑ የበርካታ የብዝሃ ህይወት ሀብቶች መኖሪያ መሆኑን ተከትሎ ጥበቃና ልማት እየተደረገለት ወደ ብሔራዊ ፓርክ እንዲያድግ ተከታታይ ጥናት እየተካሄደ ቆይቷል ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ባለስልጣኑ ጥብቅ ደኑ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መሠረት በማድረግ የጥበቃና ልማት ተግባራትን እያከናወነ መቆየቱን ገልፀዋል።
በክልላችን እና ሐገራችን ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ጋር እንዲጠበቅና እንዲለማ የጥበቃና ልማት ደንብ በማዘጋጀት ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አቅርበው ጥያቄውን እየተከታተሉ መቆየታቸውንና የመስተዳድር ምክር ቤቱም ከሐምሌ 01 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ብሔራዊ ፓርክ ሆኖ እንዲተዳደር ማፅደቁን ገልፀዋል።
ኃላፊው ተስፋሁን አለምነህ አካባቢው በብሔራዊ ፓርክነት ተመዝግቦ የቀጣይ የቱሪዝም ተስፋ እንዲሆን በመደረጉ ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ምስጋና አቅርበዋል።
ለመላው የክልሉ እና በተለይም ለሰሜን ሸዋና አካባቢው ማህበረሰብም የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት በማስተላለፍ በቀጣይ ለሚደረገው የተጠናከረ የጥበቃና ልማት ተግባራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በክልሉ አምስት ብሔራዊ ፓርኮችን እና ሰባት የማህበረሰብ ጥብቅ ስፍራዎች ላይ የጥበቃና ልማት ተግባራት እያከናወነ ሲሆን የወፍ ዋሻ ብሔራዊ ፓርክም ከሐምሌ አንድ ቀን ጀምሮ 6ኛው የብሔራዊ ፓርኮች የጥበቃና ልማት አካል ሆኖ እንደሚቀጥል ታውቋል።

