
በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበር ወረዳ አብዬ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ውስጥ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
የትምህርት ተቋሙ ግንባታ ወጪ በወረዳው አስተዳደር እና በክልሉ መንግስት በጋራ የተሸፈነ መሆኑ ተገልጿል።
በግንባታው ምርቃትና የርክክብ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የጣርማበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በጥራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ህጻናት ከእድሜያቸውና ከደረጃቸው ጋር በሚመጥን ምቹና ሳቢ በሆነ አካባቢ እንዲማሩ ያስችላቸዋል።
ህጻናት ገና በወጣትነታቸው ለትምህርት ያላቸው ፍቅርና ተነሳሽነት እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ የወላጆችንም የእፎይታ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን በመጠቆም በቀጣይም መሰል የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዋና አስተዳዳረዉ አረጋግጠዋል።
የጣርማበር ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ የሺጥላ በበኩላቸው የትምህርት ተቋሙ በይፋ ስራ መጀመሩ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህጻናትን ታላቅ ራዕይ ለማሳካት ሰፊ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
የነገዋን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት መሰረቱ ዛሬ በህጻናት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት በመሆኑ፣መንግስትና ፓርቲው ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ይህ ፕሮጀክት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
የመማሪያ ክፍሎችንና የትምህርት ተቋማትን ዘመናዊ ደረጃቸውን የጠበቁና ምቹ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ እጅግ አበረታች መሆኑን የገለጹት ደግሞ የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በድሉ ነጋሽ ናቸው።
ኃላፊው አክለውም የትምህርት ጥራት የሚጀምረው ከቅድመ-አንደኛ ደረጃ (መሰረተ-ትምህርት) በመሆኑ ይህ ተቋም ደረጃውን የጠበቀ የመማር-ማስተማር ሂደት እንዲኖር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
በተጠናቀቀው የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምርቃት ስነ-ስርዓት ላይ የወረዳው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የት/ቤቱ አመራሮች መገኘታቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል::


